የቆዳ አስም | Atopic Dermatitis
በዶ/ር ሄኖክ ዘውዱ ፤ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና የልጅ በእድሉ አይደግ መፅሀፍ ደራሲ
የቆዳ አስም (Atopic Dermatitis ) የተለመደና በተደጋጋሚ በህፃናት ላይ የሚታይ የቆዳ ህመም ነው። በአለም እስከ 30 በመቶ ህፃናት በዚህ ችግር እንደሚጠቁ ጥናቶች ያሳያሉ።
በዚህ ህመም የተጠቁ ህፃናት ሌሎች ተያያዥ የአለርጂ ህመሞች ሊኖርባቸው ይችላል
-የምግብ አለርጂ
-አስም (የአየር ቧንቧ )
-ሳይነስ (Allergic sinusitis ) አብረው ከሚታዩት ችግሮች መካከል ናቸው።
የቆዳ አስም በምን ምክንያት ይከሰታል?
ቆዳ ተፈጥሮአዊ የበሽታ መከላከያችን ነው
-ከውጪ የሚመጡ ባእድ ነገሮችን ወደሰውነታችን እንዳይገቡ ይከላከላል።
-የሠውነት ርጥበትን ይጠብቃል::
-ከኢንፌክሽን ይታደጋል።
በዚህ በቆዳ አስም በተጠቁ ህፃናት ላይ ግን ቆዳቸው ይህንን ማድረግ ይሳነዋል። ይህም ከዘረመል ለውጥ የተነሳ ነው። በዚህ ችግር የተጠቁ ህፃናት ከቤተሰባቸውም ተመሳሳይ ችግር ያለበት ሰው ይኖራል።
የቆዳ አስም ምልክቶች ምንድናቸው?
የቆዳ አስም (Atopic Dermatitis ) አብዛኛውን ጊዜ በመጀመሪያው አንድ አመት እድሜ ውስጥ ይጀምራል።
-ማሣከክ ( በተለይ ምሽት ላይ የሚብስ)
-የቆዳ መቅላት
- መቁሰልና ውሀ መቋጠር (በሁሉም የአካል ክፍል ላይ ነገር ግን ዳይፐር የሚደረግበት ቦታ ላይ ግን ሽፍታ አይኖርም)
-የቆዳ ድርቀትና መሰነጣጠቅ
-የቆዳ መሻከር( ብርጭቆ ወረቀት መምሰል)
-በተለይ በለጋ እድሜ ላይ ያሉ ህፃናት ላይ
-በጭንቅላት ቆዳ
-በፊታቸው ላይ
-በአይበሉባቸው በኩል ባለ ክርናቸው ላይ (extensor) የሚወጡ ሽፍታዎች ይታያሉ። ከፍ ያለ እድሜ ያላቸው ልጆች በውስጥ መዳፍ በኩል ከፍ ብሎ ክንዳቸው ላይ (flexor) ሽፍታው ይታያል።
*ይህ የቆዳ ህመም በቀላሉ የማይድን ሄድ መጣ የሚል ዘላቂ ህመም መሆኑን ወላጆች ሊረዱት ይገባል።
የቆዳ አስምን እንዴት ከመባባስ እንከላከል?
ይህ ህመም ያለባቸውን ልጆች አንዳንድ ምግቦችን መመገብ ሁኔታውን ያባብሳል። እንደ እንቁላል፣የላም ወተት ፣ ለውዝ ፣ አኩሪ አተር ፣ ስንዴ የመሳሰሉት ከሚያባብሱ ነገሮች ተጠቃሾች ናቸው። እንዲሁም አንዳንድ የሳሙና አይነቶችና ልብሶች ሁኔታውን ስለሚያባብሱ ወላጆች የልጆቻቸውን ሁኔታ በአንክሮ መከታተል አለባቸው።
በአግባቡ ካልታከሙ ለባክቴሪያ ኢንፌክሽን ለሌሎች አለርጂ ህመሞች ይዳርጋል። በተለይም በማሳከኩ የተነሳ ለከፍተኛ የእንቅልፍ ችግር ይጋለጣሉ። በመሆኑም ወደሀኪም በመሄድ ህክምናን መከታተል መድሀኒት መውሰድ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ወላጆች ለልጆቻቸው የቆዳቸውን ርጥበት የሚጠብቁ ቅባቶችን በመጠቀም፤ ከጥጥ የተሰሩ ልብሶችን ቢጠቀሙ፤ በሚተኙበት ጊዜ ልብስ ባለመደራረብ በዙ ሙቀትን ባለመፍጠርና ለሰውነታቸውና ለልብሳቸው ማጠብያ የሚጠቀሙትን ሳሙና በመለየት መከላከል ይችላሉ።
ቆዳ ድርቀትን መከላከል ወሳኝ የህክምናው አካል ነው። መመላለሱን ባያስቀረውም ይቀንሰዋል በመሆኑም በየእለቱ ፓራፊን ሙሉ ሰውነታቸውን መቀባት ያስፈልጋል። ገላቸውን በየቀኑ አለመታጠብ። በሳምንት 2 ቀን ሲታጠቡም የሚያለሰልሱ ሳሙናዎችን (moisturizing soap) መጠቀም ያስፈልጋል።
.jpg)

